ስለ እኛ

የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ አመሠራረት ከ1987 ጀምሮ

የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ፲፱፻፸፱ ዓ/ (.ኤአ በ1987) በሰሜን አሜሪካ ዋና ከተማ ዋሸንግተን ዲሲ መጋቤ ካህናት ከሃሊ ወንዳፈረው የተባሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን፤ባሕልና ወጓን ጠንቅቀው የሚያውቁ ፤ በውጭው ዓለም ያለውን ዘመናዊ ትምህርት በብቃት የተማሩ ኢትዮጵያዊ ሰው በመንፈሳዊ መነሳሳት እና አስተባባሪነት ጥቂት ሰዎችን ይዘው እንድትቋቋም አደረጉ።

በዚያን ጊዜ በውጭው ዓለም ካህናትን ማግኘት ቀላል ባለመሆኑ አገልግሎቱ በአንድ ካህን፣ በሁለት ዲያቆናት ከሃምሳ በማይበልጡ ምዕመናን ጊዚያዊ ቦታ ፈልገው ባገኙት ኮሎምቢያና 16ኛው መንገድ ላይ በነበረ የኪራይ ቤት በጸሎት እና በትምህርተ ወንጌል የተጀመረው አገልግሎት ከዕለት ወደ ዕለት በስደት የሚመጣው የካህናት እና ምእመናን ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ቀጣዩ ተግባር ምን መሆን እንዳለበት በየጊዜው በመሰባሰብ በሁሉም ነገር ራስን ችሎ ለመራመድ የሚያስችል ዕቅድ በማውጣት እንቅስቃሴ ተጀምሯል ።

በ፲፱፻፸፱./ (1987) ስትመሠረት በጊዜው የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በላቀ የእምነት ፍቅር በመተሳሰር የመጡ አባላትን በመመዝገብ፤ የሚያደርጉትን የገንዘብ አስተዋጽዖ በአግባቡ በመሰብሰብ እና በማጠራቀም ፤ ከዕለት ወደ ዕለት ወደ ቤተ ከርስቲያኗ የሚመጡ ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ምሑራን እየተሰበሰቡ ፤ የገንዘብ ፤ የዕውቀት ፤ የጊዜ እና በውስጧ የጎደላትን በማሟላት ቤተ ክርስቲያኗን አሁን ለደረሰችበት የዕድገት ደረጃ እንድትበቃ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

የእመቤታች የቅድስት ድንግል ማርያም ታቦተ ሕግ አመጣጥ

በዚህ ዐይነት እየተደራጁ የመጡ ኢትዮጵያውያን የተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የተሟላ አገልግሎት እንዲሠጥ ለማድረግ ተመካክረው በ1993 .ም ከቡር አባታችን ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ኃይሌ ቤተ ሰብ ለመጠየቅ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ አሜሪካ ሲመጡ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን ታቦተ ሕግ ይዘው እንዲመጡ ተወሰነ ፤ እሳቸውም አከናወኑት ፤ አሳኩት ፤ ለዚህም አበቁን ።

ራስን በመቻል በቋሚነት ቤተ ክርስቲያን ለማግኘት የተደረገ ጥረት

1987 .ም ጀምሮ በጊዚያዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ከነበረበት ቦታ ባለቤቶቹ የአጭር ጊዜ የመፈለጊያ ጊዜ ሰጥተው ቦታው እንዲለቀቅላቸው ያደረጉ ሲሆን እሑድ እሑድ አምልኮት የሚፈጸምበት ቦታ ተፈለጎ ከመታጣቱ የተነሳ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ በ16ኛውና ኒውተን መንገድ የእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በሚል የሚጠራውን ቦታ ከሌሎች ጋር በደባልነት በመግባት በአነስተኛ አደራሽ ውስጥ አዲሱ የመገልገያ ሥፍራ በመገኘቱ ከሳምንት እስከ ሳምንት ታቦተ ሕጉን ከቦታ ወደ ቦታ ማዞሩ ቀርቶ ፤ መንበር ተሠርቶ ፤ በዘወትር እና በዕለተ ሰንበት ፤ በሌሎች ቀናትም ሙሉ መንፈሳዊ አገልገሎት እንዲሰጥ ተደርጓል ። ለመጀመሪያ ጊዜ በዚሁ ሥፍራ የፍልሰታ ጾም በቅዳሴና በሰዓታት ቁመት የአካባቢው ካህናት ተራ በመግባት አገልግሎቱ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ ቆይቷል ።

ይህን የተገኘውን ቋሚ የክራይ ቦታ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለመጀመርያ ጊዜ የአካባቢው አብያተ ክርስቲያናት በኀብረት የጥምቀትን በዓል በዚሁ ሥፍራ በታላቅ ድምቀት እንዲያከብሩ ተደርጓል ። እንዲህ እያለ የቀጠለው መሰባሰብ የአካባቢውን ካህናትና ማኅበረ ምዕመናን በማሰባሰብ የእመቤታችን ቤተ ከርስቲያን የራሷ ቦታ እንዲኖራት የገንዘብ አሰባሳቢ ኮሚቴ በማቋቋም ፤ በየካቲት ወር 1996 .ም የገንዘብ ማሰባሰብ (Fund raising) ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠርቶ በዕለቱ የነበረው መንፈሳዊ ዝግጅት የቅዱስ ያሬድ ዝማሬ፤ የፍቅር ኅብረት የሰንበት ት/ቤት መዝሙርና ከመጽሕፍ ቅዱስ በአስቴር ታሪክ ላይ የተመሠረተ መንፈሳዊ ቲያትር በማቅረብ የተዋጣለትና ሕዝበ ከርስቲያኑን ያስተማረ ፤ ያስደነቀ፤ ያስደሰተ ዝግጅት ተደርጎ ዛሬ የምንገለገልበትን ቦታ ለመግዛት ያበቃን በዚያን ጊዜ የተከናወነው የገንዘብ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጻኦ ነበረው።

ይህ በእንዲህ እያለ በ1994 .  በዋሽንግተን ዲሲና አካባበው በየዓመቱ የኢትዮጵያ ስፖርት ፈደሬሽን የሚያዘገጀው ውድድር ታይሰን ኮርነር ቨርጅንያ ስለነበረ ቦታ በማስፈቀድ የገንዘብ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ተካሂዷል፤ ካህናት  ልብሰ ተክህኖ በመልበስ ፤ ባለ መጾር መስቀል በመያዝ፤ ፤ የሕዝቡን ስሜት ለማንቃት ቃጭል እያቃጨሉ ጥላ በመዘርጋት የገንዘብ ማሰብሰብ ተግባር ተከናውኗል፤ በዚህ አጋጣሚ ከተለያዩ ስቴቶች የመጡ ካህናትንና ምዕመናን ያሳተፈ የሙሉ ቀን ሲሚናርና መንፈሳዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

ቀጥሎም በዓመቱ 1995 ዓም ካልፎርንያ ግዛት በሳንዲያጎ በተደረገ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ውድድር በቦታው በመገኘት የቡና እና  የምግብ ሽያጭ የጫማ መጥረግ  በማከናወን በወቅቱ ይገኛል ተብሎ ያልታሰብ ገንዘብ በመሰብሰቡ የቤተ ክርስቲያኗን የገቢ አቅም በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አቅም ሊፈጠር በመቻሉ በአባላቱ ላይ ያለው ተስፋ ከፍ እያለ ሊመጣ ችሏል ።

ቀጥሎም በ1995 .  የኅዳር ጽዮን በዓለ ንግሥ ለመጀመርያ ጊዜ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ በተገኙበት በዚሁ ሥፍራ በታላቅ ድምቀት ሊከበር ችሏል ።

የቤተ ክርስቲያስኗን የመተዳደሪያ ደንብ (by Law) ስለማዘጋጀት

በጥር ወር 1996 .ም በጊዜው ከነበረው የአስተዳደር አመራር ጋር በመሆን ፤ ከሰ//ቤት፤ ከምግባረ ሠናይ ኮሚቴ የተውጣጡ አባላት ተሰባስበው ቀደም ሲል እንደ ውስጥ መመሪያ ሲጠቀሙበት የነበረውን በአዲስ መልክ እንዲዘጋጅ ወስኖ ረቂቁን የሚያዘጋጁ አባላትን የመደበ ሲሆን በነሐሴ ወር 1996 .ም ለሁለተኛ ጊዜ የተሻሻለ የመተዳደሪያ ደንብ (by Law) ለጠቅላላው ጉበኤ ቀርቦ ሊጸድቅ ችሏል።

በዚህ የመተዳደሪያ ደንብ (by Law) መሠረት በኅዳር ወር 1996 .  የባለአደራዎች ቦርድ ምርጫ ለመጀመርያ ጊዜ ተካሄዶ ተመራጨች ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ በተገኙበት ቃለ መኻላ ፈጽመው ሥራቸውን ጀምረዋል።

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ አሰያየም

በኅዳር ወር 1996 .ም የባለአደራው ቦርድ በአደረገው ስብሰባ መመዘኛ አውጥቶ ያሟሉትን ዶ/ር አማረ ካሳዬን የደብሩ አስተዳዳሪ አድርጎ ሰይሟል።

የቦርድ አባላት ምርጫ

የመጀመሪያዎች የቦርድ አባለት የነበሩ

    1. ክቡር አባታችን ሊቀ ሊቃውንት ወርቅነህ ኃይሌ ካህናቱን በመወከል
    2. /ር አማረ ካሣዬ በአለቃነት
    3. ርእሰ ደብር አብርሃም ሀ/ሥላሴ
    4. መጋቤ ካህናት ከሃሊ ወንድአፈረው በመሥራችነት
    5. መጋቤ ሥርዓት አለምሸት ሙሉነህ
    6. /ር አክሊሉ ሀብቴ
    7. አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ
    8. አቶ ዳኛቸው ግዛው
    9. /ሮ ፋሲካ አስራት
    10. 10.አቶ ፍሬው ቡልቡላ
    11. 11./ሮ ብርሃኔ ወማርያም ነበሩ።

ቤተ ክርስቲያኗ የራሷ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ (By law) ፣ የሠራተኞች መተዳደሪያ ደንብ (Personnel Manual) ፣፣የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር መምሪያ (Accounting Manual) ፣ የአስተዳደር መዋቅር (Organizational Structure) እና ሌሎች ለአስተዳደሩና ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ መጠናከርና ሥርዓት መያዝ የሚረዱ ሠነዶችን በማዘጋጀትና እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ቤተ ክርስቲያኗ እድገት በየጊዜው በማሻሻል አግልግሎቷን በሕግና በሥርዓት ስታከናውን ቆይታለች። አሁንም እያከናወነች ትገኛልች። እኤአ በ2018 ዓም የቤተ ክርስቲያኗን እድገትና የአገልግሎት ስፋት እንዲመጥን ተደርጎ ለሁተኛ ጊዜ የተሻሻለው የመተዳደሪያ ደንብ በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቆ አገልግሎት ላይ ውሏል። በተመሳሳይ መልኩ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ መዋቅር የቤተ ክርስቲያኗን የአገልግሎት ስፋት ባገናዘበ መልኩ በመሻሻል ላይ ይገኛል ። ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው የሠራተኞችን ቁጥር ሊያስተዳድር የሚችል፣ የአሜሪካን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያንን የሠራተኞችን መተዳደሪያ ደንብ ያጣጣመ የሠራተኞች መተዳደሪያ ደንብም በዚሁ ዓመት ተሻሽሎ በተግባር ላይ ይውላል።

በካህናትና በምዕመናን፣ በፍቅር ሕብረት የሰንበት ት/ቤት ወጣቶቸ በእምነት በጠነከረ ፍቅርና አንድነት በፈንድ ሬይዚንግ መጠነኛ ገንዘብ በማሰባሰብ ኢኤአ ዛሬ የምንገለገልበት ቦታ የተገኝ የተገዛ??ሲሆን በዚህም የቦታ የንብረት ባለቤት መሆን ተጀመረ። ቀጥሎም እኤአ በ1998 14ኛው መንገድ አዋሳኝ ያለው የመኪና ማቆሚያ ተገዛ። በማካታተልም ለእንግዶች ማረፊያ ቤቱ እንዲሆን ተብሎ በ14ኛውና በዲኬተር መንገድ ያለው ቤት ተገዛ። በመጨረሻም እ..አ በ2004 ዓም አሁን በደጀ ሰላምነት የምንገለገልበት ቦታ ተገዛ። ቤተ ክርስቲያኗ እ..አ ከ1987 እስከ 2004 /ም ድረስ ይዞታዎች በመግዛት በአሁኑ ሰዓት በዋሽንግተን ዲሲ መሐል ላይ ከባንክ እዳ ነጻ የሆን የ61000 ስኩየር ጫማ ይዞታ ባለቤት ለመሆን በቅታልች።

 

የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎቶች

መንፈሳዊ አገልግሎት

ቤተ ክርስቲያኗ የምትሰጠው መንፈሳዊና ማሕበራዊ አገልግሎትም በተመሳሳይ መልኩ እያደገ መጥቶ በሦስት አገልጋዮች የተጀመረው የቤተ ክርስቲያኗ አገልግሎት ዛሬ ከ20 በላይ ካህናትና ሊቃውንት ያገለግሉባታል። በቁጥር 50 ያህል ሆነው የጀመሯት ምዕመናን ዛሬ እጅግ በዝተው ይገኛሉ ። የመንፈሳዊ አገልግሎቱ ሰፍቶ በዕለተ ሰንበት ብቻ የነበረው የቅዳሴ አገልግሎት ዛሬ በየወሩ የእመቤታችን ፤ የጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ ዓመታዊ የንግሥ በዓላት፤ በዓቢይ ጾም እሑድ ሳይቆጠር ዓርብ እና ቅዳሜን፤ ጾመ ፍልሰታን 16 ቀን የቅዳሴ አግልግሎት ይሰጣል።

በዓመት ሰባት የንግሥ በዓላት በማኅሌት ታጅበው በደመቀ ሁኔታ ይከበራሉ። ዓበይት በዓላትም እንዲሁ። በየሳምነቱ ከ5 -10 የሚደርሱ ሕጻናት ሀብተ ውልድና ስም ክርስትና ይቀበላሉ።

ስብከተ ወንጌል

በመደበኛ ረቡዕ እና ዓርብ ፤ እሑድ እና በየወሩ የእመቤታችን ፤ የጻድቁ ተክለ ሃይማኖት ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ፤ ዓመታዊ የንግሥ በዓላት፤ በዓቢይ ጾም ፤ ጾመ ፍልሰታን 16 ቀን  የውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ አግልግሎት ይሰጣል በስሙነ ሕማማት የኪዳን እና የትምህርተ ኅቡዓት ትርጓሜ አገልግሎት ይሰጣል። በተጨማሪም ዘመን በወለደው ቴክኖሎጂ በመታገዝ በየቤታቸው ሆነው ተከታትይ ትምህርት በደብሩ ስብከተ ወንጌል ኃላፊ እና ሌሎችም መምህራንን በመጋበዝ እየተሰጠ ይገኛል።

የምክረ ካህን አገልግሎት

ካህናት አባቶች ለማነጋገር በየቀኑ ??የሚገኙ አንድ ካህን በቋሚነት ቢሮ የሚውሉ ሲሆን ሌሎች ካህናት ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር በሚመቻቸው ሰዓት ቀጠሮ በመያዝ አስተዳደር ጽ/ቤት በሚያዘጋጅላቸው ቢሮ ውስጥ ውይይት ያደርጋሉ ።

የአስተዳደር /ቤቱ

ጉዳይ ለማስፈጸም አስተዳደር ቢሮ መምጣት ለሚፈልጉ ቤተ ክርስቲያኗ በሳምንት ሰባት ቀናት ክፍት ስትሆን ከመንፈሳዊ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ክፍያዎችን ፤ በርካታ መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ለሚፈልጉ ምዕመናን በተሟላ መልክ እንዲያገኙ ሆኖ የተዋቀረ አስተዳደር ያላት ደብር ናት፡፡

የቤተ ክርስቲያኗን የውስጥ አሠራር የአመራር ሠንሰለት አሥራ ስድስት የሚደርሱ በልዩ ልዩ የሥራ ድርሻ የተዋቅሩ ንዑሳን ኮሚቴ ያላት ሲሆን እያንዳንዳቸው ተጠሪነታቸው ለደብሩ አስተዳደር የሆነ የራሳቸው የውስጥ መመሪያ የተዘጋጀላቸው 5 እና ከዛ በላይ እንዳስፈላጊነቱ በኮሚቴ ተዋቅረው በ2 ዓመት የምርጫ ዘመን እየተቀያየሩ የሚያጋለግሏት የተደራጀች ደብር ናት ።

ይህ ሁሉ ፍሬ በእግዚአብሔር ፈቃድ፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ በካህናትና በምዕመናን ጸሎት እስካሁኗ ሰዓት ስላደርሰን ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን የአዲሱን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመገንባት የዲዛይን እና ስትራክቸር ጥናት ለመጀመር ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ተቀናጅተን በመሥራት ላይ ስንሆን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታገዝ ኃይላችንን አንድ በማድረግ ለውጥ የሚታይበት ሥራ ለማሳየት በመፋጠን ላይ እንገኛለን ።

የርእሰ አድባራት ደብረ ሰላም ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንአስቀድሞ አብ መሠረታት፣ ወልድ ገነባት፣ መንፈስ ቅዱስ ፈጸማት  የተባለላት በሰዎች እና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን መልካም ግንኙነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ እና ቀናና አክብራ እና አቅጣጫዋን ጠብቃ በሥርዓት ወደ ክፍታ እየተጓዘች ያለች ታላቅ ደብር ስለሆነች የሁላችሁም ጸሎት እና ልመና ዘወትር እንዲያግዘን  የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከሁላችን ጋር ይሁን፤ ችርነቱ ወሰን የሌለው አምላክ ይርዳን አሜን ።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር።