ጥምቀት
ጥምቀት (Mystery of Baptism) የሚለው ቃል "አጥመቀ" (አጠመቀ) ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም በተከማቸ ውሃ ውስጥ መነከር፡ መዘፈቅ፡ ገብቶ መውጣት ማለት ነው። ምስጢረ ጥምቀት በምስጢራዊ (በሃይማኖታዊ) ፍቺው በተጸለየበት ውሃ (ማየ ኅይወት) ውስጥ በሥላሴ (በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ) ስም ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ብሎ የመውጣት ሂደት ነው (ማቴ 28፡19)። ጥምቀት "የክርስትና መግቢያ በር" ናት፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች ምስጢራት ስለሚቀድምና ለእነርሱም መፈጸም ቅድመ ሁኔታ ስለሆነ ነው፡፡ ጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ተወልደን የሥላሴን ልጅነት የምናገኝበት (ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና) ምሥጢር ነው። ሰው ከሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ለመካፈል አስቀድሞ መጠመቅና ከማኅበረ ክርስቲያን መደመር አለበት፡፡ ስለዚህም ምስጢረ ጥምቀት ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት እንዲሁም ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ የእምነታችን መሠረትም፣ የጸጋ ልጅነት የሚገኝበትም ምስጢር ነውና ከሁለቱም ይመደባል፡፡
የጥምቀት አመሠራረት
የምሥጢረ ጥምቀት መሥራች ራሱ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ነገር ግን ከጌታችን ጥምቀት በፊት አይሁድ ለመንጻትና ለኃጢአት ሥርየት (ይቅርታ) የሚጠመቁት "ጥምቀት" ነበራቸው፡፡ ይኸውም እግዚአብሔር በረድኤት የሚገለጥባቸው የተቀደሱ ዕለታትና ቦታዎች ሁሉ ሰውነትንና ልብስን ማጠብ የእግዚአብሔር ቤት ማገልገያ የሆኑ ዕቃዎችን ሁሉ ማጠብ ማንጻት ሥርዓትና ልማድ ነበር፡፡ ይህም የእግዚአብሔርም ፈቃድ ያለበት አሠራር ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቤት ከመቅረባቸውና ለተቀደሰው አገልግሎት ከመግባታቸው አስቀድመው እግሮቻቸውንና እጆቻቸውን የመታጠብ ግዴታም ነበራቸው፡፡ ሰውነታቸውን ከአፍአዊ (ከውጫዊ) እድፍ በማጠብና ንጹሕ በማድረግ በባሕርይ ንጹሕና ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ውስጣዊ ሕይወትን ንጹሕ አድርጎ የመቅረብን ሥርዓትና ምሥጢር የሚያመለክት መንፈሳዊ ሥርዓት ነበር፡፡
ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀትን የመሠረተው በሦስት መንገድ ነው። መጀመሪያ በተግባር ራሱ ተጠምቆ እንድንጠመቅ አስተምሮናል፤ አርአያም ሆኖናል (ማቴ 3፡13)፡፡ ሁለተኛም በትምህርቱ "ያመነ የተጠመቀ ይድናል" (ማር 16፡16) እንዲሁም "እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔር መንግሥት ሊያይ አይችልም" (ዮሐ 3፡3-6) በማለት ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ሦስተኛም ለቅዱሳን ሐዋርያት በሰጣቸው ትዕዛዝ "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው" (ማቴ 28፡19-20) በማለት ምስጢረ ጥምቀትን መስርቶልናል። ይህንንም መሠረት በማድረግ ሃይማኖታቸው የቀና ቅዱሳን አባቶች "ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን" በማለት መሠረተ እምነትን ደንግገዋል፡፡
የጥምቀት አስፈላጊነት
በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከኒቂያ ጉባኤ በኋላ ከተነሱት አባቶች አንዱ "በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም" (ራእይ 20:6) የሚለውን የወንጌላዊው ዮሐንስን አባባል በተረጎመበት የእግዚአብሔር ከተማ በሚለው መጽሐፉ ላይ "ፊተኛው ትንሣኤ" የተባለው ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምናገኝበት ጥምቀት እንደሆነ ገልጿል። ክርስቶስን መሠረት ያደረገ እምነት ሁሉ "ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም" (ዮሐ. 3፡3) የሚለው የጌታ ትምህርት መመሪያው ሊሆን ግድ ነው፡፡ ጌታችን እንዳስተማረውም ያለጥምቀት ድኅነት የለም፡፡ በምስጢረ ጥምቀት በሚታየው አገልግሎት የሚገኘው የማይታይ ጸጋ ግን ብዙ ነው፡፡ የሚከተሉት በጥምቀት የሚገኙ የማይታዩ ጸጋዎች ናቸው።
ድኅነት "ያመነ የተጠመቀ ይድናል" (ማር. 16፡16)
የድኅነት ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ እንደተናገረው ዘላለማዊ ድኅነትን ለማግኘት የሚሻ ሁሉ ወልድ ዋሕድ በምትለው ሃይማኖት አምኖ መጠመቅ ግድ ይለዋል፡፡ ስለዚህም ጌታችን ከሙታን ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ "ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል" (ማር 16፡16) በማለት በጥምቀት ድኅነት እንደሚገኝ አረጋግጧል፡፡ ከጌታ ከቃሉ የተማረ ቅዱስ ጴጥሮስ የመምህሩን ትምህርት መሠረት አድርጎ "ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍስ በውኃ የዳኑበት መርከብ ሲዘጋጅ፤ የእግዚአብሔር ትዕግስት በኖኅ ዘመን በቆየ ጊዜ ቀድሞ አልታዘዙም፡፡ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቀት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም" ብሏል፡፡ (1ኛ ጴጥ. 3፡20-21)፡፡ ኖኅና ቤተሰቡ የዳኑበት ውኃ ምሳሌነቱ የጥምቀት መሆኑን ገልጾ አሁንም በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ሁሉ በጥምቀት ድኅነትን እንደሚያገኙ በግልጽ ቃል ተናግሯል፡፡ መዳን ስንል የእግዚአብሔርን መንግሥት ወርሶ የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆን ማለት ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሌሊት የትምህርት መርሐ ግብር ትምህርቱን በተመስጦ ኅሊና በሰቂለ ልቡና ይከታተል ለነበረው ለኒቆዲሞስ የድኅነት በሩ ጥምቀት እንደሆነ ገልጾለታል "እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ ይችልም" (ዮሐ. 3፡5)፡፡ ይህ ታላቅ ቃልም ጥምቀት ለድኅነት አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል፡፡
ዳግም ልደት "ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም" (ዮሐ. 3፡5)
ጥምቀትን ዳግም ልደት ያስባለው ከሥጋ ልደት የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ በአዳምና በሔዋን ስህተት ምክንያት አጥተነው የነበረውን የልጅነት ጸጋ የምናስመልሰው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው፡፡ ዳግም ከሥላሴ የምንወለደው በውኃ በምናደርገው ጥምቀት ነው፡፡ ጌታችን "እውነት እውነት እልሃለሁ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት አይገባም" (ዮሐ. 3፡5) በማለት ለኒቆዲሞስ መናገሩን ልብ ይሏል፡፡ ጌታችን እንደተናገረው ጥምቀት የልጅነትን ጸጋ የምናገኝበት ምሥጢር ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጥምቀት ዳግም ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ታላቅ ምሥጢር መሆኑን እንዲህ ሲል አስተምሯል "ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም" (1ኛ ጴጥ. 1፡23)፡፡ ይህ ቃል ጥምቀት የዘላለም ሕይወት እንደሚያሰጥ ያሳያል፡፡ ጌታችን በግልጽ ቃል እንደተናገረው የማይጠፋው የልጅነት ጸጋ የሚገኘው በውኃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ በማድረግ በሚፈጸመው ገቢር እንጂ አንዳንዶች ከልቦናቸው አንቅተው እንደሚናገሩት ቃለ ወንጌልን በመስማት ብቻ የሚገኝ አይደለም፡፡ በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች ሆነን መንግስቱንም እንወርሳለን፡፡
ሥርየተ ኃጢአት "ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኃጢአት" (ጸሎተ ሃይማኖት)
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ባወጡት አንቀጸ ሃይማኖት ላይ ካሰፈሩት አንቀጽ አንዱ በጥምቀት ሥርየተ ኃጢአት እንደሚገኝ "ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለሥርየተ ኀጢአት፣ ኀጢአትን በምታስተሠርይ በአንዲት ጥምቀት እናምናለን" የሚለው ነው፡፡ እነዚህ አባቶች በቅዱስ መጽሐፍ የሰፈረውን በአንዳንድ የቤተክርስቲያን የውስጥ ጠላቶች አማካይነት ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኮ የገባን የስህተት ትምህርት ለማጥራት፣ እምነትን ለማጽናትና ምእመናንን ከውዥንብር ለመታደግ አንቀጸ ሃይማኖትን ወስነዋል፡፡ ይህ የአበው ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ መሆኑን ከብዙ ማስረጃዎች የምንገነዘበው እውነታ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡ በድንቅ አጠራሩ ለአገልግሎት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስ ከኃጢአቱ ይነጻ ዘንድ "አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ" መባሉን አስተውሉ (የሐዋ. ሥራ 22፡16)፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሣ ተሰብስበው ለነበሩት በትምህርቱ ልቡናቸው በተነካ ጊዜ "ምን እናድርግ?" ብለው ሲጠይቁት የመለሰላቸው "ንስሐ ግቡ ኃጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ" ብሏቸው ነበር (የሐዋ. ሥራ 2፡37-38)፡፡ ይህ ታዲያ ከሌላ በረት ለመጡ በጎች እንጂ በበረቱ ተወልደው በበረቱ ላደጉት በጎች አይደለም፡፡ "በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ" ማለቱ የእርሱን የባሕርይ አምላክነት ለመግለጽ እና ዓለም እንዲቀበለው ለማስተማር እንጂ ጥምቀት መፈጸም የሚገባው በሥላሴ ስም መሆኑን ጌታችን ራሱ አስተምሯል (ማቴ 28፡19)፡፡ "ወነአምን በአሐቲ ጥምቀት ለስርየተ ኃጢአት" በሚለው ንባብ ውስጥ ያለችው "ስርየተ ኃጢአት" የምትል 'ነባር' ኃጢአትን አመላካች ሐረግ የምታመለከተው ካደጉና ከጎለመሱ በኋላ ተምረው፣ አምነው፣ አመክሮ (የፈተና ጊዜ) አልፈው ለጥምቀተ ክርስትና የበቁ ንዑሰ ክርስቲያኖችን እንጂ ሕጻናትን ወይም ጥንተ አብሶን አያመለክትም፡፡
ክርስቶስን መምሰል "ጥምቀት ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበትና በትንሣኤው የምንተባበርበት ነው" (ሮሜ 6፡3-4)
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ የተጠመቅን ሁላችን ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ እንደ ተጠመቅን አታውቁምን? እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደተነሣ እንዲሁ እኛ በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን" (ሮሜ. 6፡3-4) በማለት በጥምቀት ክርስቶስን እንደምንመስለው ተናግሯል፡፡ ማጥመቅ በፈሳሽ ውኃ ነው፤ ጥልቅ ውኃ በማይገኝበት ጊዜ ግን ውኃ በሞላበት ገንዳ ይፈጸማል፡፡ ይህም ካልሆነ ውኃ ቀድቶ የተጠማቂውን መላ አካል ውኃው እንዲያገኘው በማድረግ በእጅ እየታፈኑ ያጠምቁታል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የተጠማቂው አካል በውኃ እንዲጠልቅ መደረጉ "ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን" (ሮሜ. 6፡4) የሚለውን በገቢር ለመግለጽ ነው፡፡ እንዲሁም ተጠማቂው ከውኃ ውስጥ ብቅ ማለቱ "በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር ሥራ በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሳችሁ" (ቆላ. 2፡12) ያለውን እንዲሁ በድርጊት ለማሳየት ነው፡፡
አጥማቂው ካህን "አጠምቀከ/ኪ በሥመ አብ አጠምቀከ/ኪ በሥመ ወልድ አጠምቀከ/ኪ በሥመ መንፈስ ቅዱስ" እያለ ሦስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ እያደረገ ድርጊቱን ሦስት ጊዜ መፈጸሙ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት አምኖ መጠመቁን ለማጠየቅ ሲሆን እንዲሁም የጌታን ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በመቃብር አድሮ መነሳቱንና ተጠማቂዎችም ኋላ በትንሣኤ ዘጉባኤ "ንቃ መዋቲ" የሚለው አዋጅ ሦስት ጊዜ በሚታወጅበት ጊዜ በቀዋሚ አካል በምትናገር አንደበት ከራስ ጠጉራቸው እስከ እግር ጥፍራቸው ከቁጥር ሳይጎድሉ ከሰውነታቸው ሳይከፈሉ ወንድ በአቅመ አዳም ሴት በአቅመ ሔዋን መነሳታቸውን ለማዘከር ነው፡፡ ስለዚህ ጥምቀት "ከክርሰቶስ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንድንኖር እናምናለን" (ሮሜ. 6፡8) በሚለው የሐዋርያው ቃለ ትምህርት መሠረት ጥምቀት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሞቱ የምንመስልበት በትንሣኤውም የምንተባበርበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡
የክርስቶስ አካል መሆን "ጥምቀት የክርስቶስ አካል መሆናችን የሚረጋገጥበት ነው" (ገላ 3፡27)
በዘመነ ብሉይ የአብርሃም ወገኖች የአብርሃም ልጆች መሆናቸው ይረጋገጥ የነበረው በግዝረት ነበር፡፡ ግዝረት በኦሪቱ የእግዚአብሔር ሕዝብ መለያ ነበር፡፡ ያልተገረዘ ሁሉ ከሕዝቡ ተለይቶ እንዲጠፋ የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ነበር (ዘፍ. 17፡14)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በአምሳልነት ሲፈጸም የኖረው ግዝረት በዘመነ ሐዲስ በጥምቀት መተካቱን "በክርስቶስ ገዛሪነት የኃጢአትን ሕዋስ ሰንኮፍ ቆርጦ በመጣል ሰው ሰራሽ ያይደለ ግዝረትን የተገዘራችሁበት፤ በጥምቀት ከእሱ ጋር ተቀበራችሁ ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትም በሃይማኖት ከእሱ ጋር ለመኖር በእስዋ ተነሣችሁ" (ቆላ. 2፡11-12) በማለት አበክሮ ያስገነዝባል፡፡ ግዝረት ለሕዝበ እግዚአብሔር የአብርሃም የቃል ኪዳን ተሳታፊዎች የመሆናቸው መለያ ምልክት እንደነበር ሁሉ ጥምቀት ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ የጸጋው ግምጃ ቤት ከሆነችው ቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ጸጋ ተሳታፊ ያደርጋቸዋል፡፡ በጥምቀት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ "ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና" (ገላ. 3፡27) በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው በጥምቀት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ እንሆናለን፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር ያደሰውን አዲሱን ሰውነት የምንለብሰውና የክርስቶስ ተከታዮች የምንሆነው በጥምቀት ነው፡፡
የጥምቀት አከፋፈል (ዓይነቶች)
የንስሐ ጥምቀት
የንስሐ ጥምቀት ልጅነትን ላገኙ ሰዎች ሕይወት ፈተና ለሚደርስባቸው ድካምና ጉስቁልና ፈውስ እንዲሆን የሚሰጥ ሊደጋገምም የሚችል የጥምቀት ዓይነት ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ያጠምቀው የነበረ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ማሳያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ዮሐንስ ጥምቀትን ያጠምቅ የነበረ ቢሆንም የዮሐንስ ጥምቀት ልጅነትን የሚያሰጥ ጥምቀት አልነበረም። የዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ጥምቀት ነበር። የዮሐንስ ጥምቀትን አቅምንም ሊቃውንተ ቤተ ክርስትያን እንዲህ ሲሉ ይገልጹታል። እድፍ ቆሻሻ የያዘው ልብስ በውኃ ታጥቦ ነጽቶ ሽቱ ይርከፈከፍበታል። ገላም ሲያድፍ በውኃ ታጥቦ ጽዱ ልብስ ይለብሳል። እንደዚሁም ሁሉ የዮሐንስ ጥምቀት ተጠማቂዎቹ ኋላ በክርስቶስ ጥምቀት የሚሰጠውን መንፈስ ቅዱስን ለመቀበል በቅተው እንዲገኙ ከኃጢአት መለየታቸውንና ተለየን ማለታቸውን የሚገልጽ ምልክት ነበር። ራሱም አንዲህ ሲል መስክሯል "እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ …ከኔ በኋላ የሚመጣው እርሱ ግን በእሳት ያጠምቃችኋል.." (ማር 1፡4-8 ማቴ 3፡11 ሉቃ 3፡16 ሐዋ 19፡4)፡፡ በነቢዩ ሕዝቅኤልም "ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ፤ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ። መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ። ለአባቶቻችሁም በሰጠኋት ምድር ትኖራላችሁ፤ ሕዝብም ትሆኑኛላችሁ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ" (ሕዝ 36፡25-28) ተብሎ የተነገረውም የንስሐ ጥምቀትን የሚያመለክት ነው፡፡
የልጅነት ጥምቀት
አስቀድመን በሥጋ ከእናትና አባታችን በዘር በሩካቤ እንደተወለድንና የሥጋ ልጅነትን እንዳገኘን ሁሉ በማየ ገቦ ስንጠመቅ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ እንወለዳለን፡፡ ይህንን አስመልክቶ ጌታችን "ከሥጋ የሚወለድ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስ የሚወለድ መንፈስ ነው" ብሎ ከማስተማሩ በፊት "ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም" በማለት (ዮሐ. 3፥3 እና 6) በምሥጢረ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ስለመገኘቱ አስተምሯል፡፡ ሐዋርያውም በጥምቀት ስላገኘነው የልጅነት ጸጋ አስመልክቶ ሲናገር "አባ አባት ብለን የምንጮኸበትን (የምንጣራበትን) የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈስ ጋር ይመሰክራል" ብሏል (ሮሜ. 8፥15-16)፡፡ ጌታችንም ለተቀበሉት ሁሉ በስሙም ላመኑበት በጠቅላላው የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጥቷቸዋል፡፡ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አለመወለዳቸው ተገልጿል (ዮሐ. 1፥11-13)፡፡ እንግዲህ እኛ ክርስቲያኖች ሁለት ልደታት እንዳሉን እናስብ፡፡ ይኸውም መጀመሪያው ከሥጋ እናትና አባታችን የተወለድነው ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከእግዚአብሔር የምንወለደው ነው፡፡ ከተወለድን በኋላ እድገታችን በሁለቱም ወገን መሆን ያስፈልጋዋል፡፡ ሰው ሥጋዊም መንፈሳዊም ነውና፡፡ (ገላ 3፡26 ፡ ቲቶ 3፡5 ፡ 1ኛጴጥ 1፡23)
የልጅነት ጥምቀት በምን ይፈጸማል?
ልጅነት የምታሰጠዋ ጥምቀት አንዲት ናት (ኤፌ 4፡4-5)፡፡ ነገር ግን በሦስት ዋና ዋና መንገዶች ልትፈጸም ትችላለች። የውሃ ጥምቀት በካህናት አማካኝነት በተጸለየበት ውሃ ውስጥ በሥላሴ ስም ተጠምቀን በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከእግዚአብሔር የምንወለድበት ነው (ዮሐ 3፡3-6)፡፡ ጥምቀት በመርህ ደረጃ በውኃ የሚፈጸም ነው፡፡ ውኃው በጸሎት በተባረከ ጊዜ ልጅነትን የሚሰጥ የእግዚአብሔር መንፈስ ስለሚያድርበት በእምነት ሆኖ በውኃ የሚጠመቅ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ይወለዳል፡፡ ጥምቀት የእግዚአብሔር ቸርነት መገለጫ ነው፡፡ ማንም ሰው ደሃ እንኳ ቢሆን ቢያንስ ውኃ ይኖረዋልና በጸጋ ከእግዚአብሔር እንወለድ ዘንድ በውኃ መጠመቅ ይገባል፡፡ በውኃ መጠመቅ እየቻሉ መጠመቅን እንደተራ ነገር አድርገው የሚያቃልሉ ሰዎች ኤሳው እንዳቃለላት ብኩርና ባለማወቅ የእግዚአብሔርን ጸጋ ያቃልላሉ፡ በአንጻሩ ደግሞ በፍጹም ልብ የክርስትናን ትምህርት አምነው ከመጠመቃቸው በፊት በሰማዕትነት የሚያርፉ ሰማዕታት እግዚአብሔር ባወቀ የልጅነትን ጥምቀት ከመንፈስ ቅዱስ ወይም ከእሳት ይቀበላሉ፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ማለት ደግሞ በውሃ ሳንጠመቅ እግዚአብሔር በፍቃዱ ጸጋውን በመላክ የሚሰጠን ልደት ነው። ለዚህም ምሳሌ የሚሆነን ቅዱሳን ሐዋርያት የተጠመቁት ጥምቀት ነው (ሉቃ 3፡16 ፡ ሐዋ 1፡5 ፡ ሐዋ 2፡1-4 ፡ 1ኛ ቆሮ 12፡13)፡፡ ሦስተኛው የደም ጥምቀት ሲሆን ይህ የሰማዕታት የጥምቀት ዓይነት ነው። የክርስትናን እምነት በመማር ላይ ሳሉ ወይም ተምረው ሳይጠመቁ ወይም ሁለቱንም ሳያውቁ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ብለው መሥዋዕት መሆናቸውን ተመልክተው "ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ አምላክ ነው፤ የክርስቲያኖች እምነት እውነተኛ ነው" በማለት መስክረው በሰማዕትነት የሚሞቱ ሰዎች ደማቸው (ስቃያቸው) በእግዚአብሔር ቸርነት እንደ ጥምቀት ይቆጠርላቸዋል። ልጅነትን ያገኙበታል፤ ኃጢአታቸውም ይሰረይላቸዋል።
ጥምቀት እንዴት ይፈጸማል?
ተጠማቂው ንዑሰ ክርስቲያን ከሆነ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርቶችን ተምሮ እምነቱ የተመሰከረለት መሆን አለበት። ሕጻናት የሆኑ እንደሆኑ ግን ለሕጻናቱ የክርስትና እናትና አባት ሊሆኑ የመጡት ሰዎች ስለሕጻናቱ እምነት መስክረውላቸው እንዲጠመቁ ይደረጋል። በሚጠመቅበት ጊዜ በውሃ ውስጥ ሶስት ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማለት አለበት፤ የክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ ምሳሌ ነውና። ተጠማቂው የሚጠመቀው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው (ማቴ 28፥19)። ተጠማቂዎች ባለትዳሮች ከሆኑና ቤተሰብም ካላቸው ሁሉም ተምረው አምነው በአንድነት መጠመቅ አለባቸው። ከተጠመቀ በኋላ መቁረብ (ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል) ይገባል። ይህ ካልሆነ ጥምቀቱ ህያው አይሆንም።
እንዲያጠምቁ ስልጣን ያላቸው ከክህነት ደረጃዎች ውስጥ ኢጲስቆጶስና ቀሳውስት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማጥመቅ ስልጣንን የሰጠው ለአስራ አንዱ ሐዋርያት ብቻ ስለሆነ ነው (ማቴ 28፡19)፡፡ ዲያቆናት እንዲያጠምቁ አልተፈቀደላቸውም (ማቴ 28፡19 እና ፍት ነገ አንቀጽ 3)። ክህነት በሌለው ሰው የተከናወነ ጥምቀት እንደ እጥበት እንጂ እንደ ጥምቀት አይቆጠርም፡፡ በዚህ መንገድ "የተጠመቀ" ሰው ልጅነት የምታስገኘዋን እውነተኛዋን ጥምቀት መጠመቅ አለበት፡፡ ጥምቀት በመድፈቅ ወይም በመንከር ነው እንጂ በመርጨት (በንዝሐት) አይፈጸምም፡፡ ምሳሌውን፣ ምስጢሩንና ሥርዓቱን ያፋልሳልና፡፡ ጥምቀት ማለት መነከር ማለት ስለሆነ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን ያመለክታል፡፡ ስለዚህም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሦስት ጊዜ ውኃ ውስት ገብቶ በመውጣት ይከናወናል (ማቴ 28፡19)፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም የተገለጠው በመንከር የተከናወነው ጥምቀት ነው፡፡
በሐዋርያት ሥራ ላይ "ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና (ሐዋ 8፡38-39)" በሚለው ቃል ውስጥ "ከውኃ ከወጡ በኋላ" የሚለው የሚያመለክተው ጃንደረባው የተጠመቀው ውኃ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ነው፡፡ "እንግዲህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሙታን እንደ ተነሣ እንዲሁ እኛም በአዲስ ሕይወት እንድንመላለስ፥ ከሞቱ ጋር አንድ እንሆን ዘንድ በጥምቀት ከእርሱ ጋር ተቀበርን። ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን (ሮሜ 6፡4-5 ቆላ 2፡12)" በሚለው ቃል ውስጥ መቀበር መቃብር ውስጥ መግባትን፣ ትንሣኤ ደግሞ ከመቃብር መውጣትን እንደሚያመለክት ጥምቀትም በውኃ ውስጥ ገብቶ (በመነከር) መውጣትን ይጠይቃል፡፡
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ "እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም (ቲቶ 3፡5)" እንዲሁም "አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ (ሐዋ 22፡16)" ተብሎ ለሳውል በተነገረው ቃል ውስጥ "መታጠብ" ሰውነትን በሙሉ ነውና ጥምቀትም በመነከር ይከናወናል፡፡ በአራቱም ወንጌላት የጌታችን ጥምቀትም በውኃ ውስጥ ገብቶ በመውጣት መሆኑ ተጽፏል፡፡ "ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም፥ ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ (ማቴ 3፡16)" በሚለው ቃል ውስጥ "ከውኃ ወጣ" የሚለው የጌታችን ጥምቀት የተከናወነው በመነከር እንደነበር ያሳያል፡፡ መረጨት ወይም ማፍስስ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን አይጠይቅምና፡፡ በተጨማሪም በሥጋ መወለድ በእናት ማኅፀን ውስጥ ቆይቶ መውጣትን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ "ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መወለድም" እንዲሁ ውኃ ውስጥ ገብቶ መውጣትን (መነከርን) ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ነው ጥምቀት "ዳግመኛ መወለድ" የተባለው (ዮሐ 3፡3)፡፡
ስመ ክርስትና (የክርስትና ስም)
ስም አንድ ሰው ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት ነው። ሰው ከእናትና ከአባቱ ሲወለድ ስም እንደሚወጣለት ሁሉ በጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ሲወለድም ስም ይወጣለታል፡፡ ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ሁለት ዓይነት ስሞች ሊኖሩት ይችላል። አባትና እናት የሚያወጡለት ስም የተጸውኦ ስም ይባላል፡፡ በጥምቀት ጊዜ የሚወጣለት ስም ደግሞ የክርስትና ስም ይባላል፡፡ በጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ይገኝበታል፡፡ በክርስቶስ የሚያምን ሰው ክርስቲያን ሲባል እምነቱ ደግሞ ክርስትና ይባላል። ክርስቲያን ማለት የክርስቶስ ወገን የሆነ ማለት ነው። በመሆኑም በክርስቶስ አምነን በሥላሴ ስም መጠመቃችንን የሚገልጸው ስም ስመ ክርስትና ይባላል። ስያሜውም ተጠማቂው ከተጠመቀበት ዕለት ጋር ተያይዞ ሊሰየም ይችላል። በመንፈሳዊ አገልግሎት ስንሳተፍ ስመ ክርስትናችንን እንጠቀማለን፡፡ የክርስትና ስም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትውፊት ያለው ነው፡፡ ይህም እግዚአብሔር አብራምን አብርሃም፣ ያዕቆብን እስራኤል፣ ሰምዖንን ጴጥሮስ፣ ሳውልን ጳውሎስ እንዲባል እንዳደረገው ያለ ነው፡፡
ለጥምቀት የተወሰነ ዕድሜ
በሐዋርያት ስብከት ያመኑና በማንኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሁሉ ይጠመቁ ነበር (የሐ ሥራ 16፡15 1ቆሮ 1፡15)። በኋላ ግን ወላጆቻቸው ሊያስተምሯቸው ቃል እየገቡ ልጆቻቸውን ወንዶችን በአርባ ሴቶችን በሰማንያ ቀናቸው ማጥመቅ ተጀመረ። ለዚህም መሠረቱ የእስራኤል ልጆች በተወለዱ ወንድ በአርባ ሴት በሰማንያ ቀናቸው ወላጆቻቸው መባዕ (ስጦታ) ይዘውላቸው ወደ ቤተ መቅደስ እየሄዱ በእስራኤልነት (የዜግነት) መዝገብ እያስመዘገቡ የተስፋዋ ምድር ከነዓን ባለመብቶች (ወራሾች) ያደርጓቸው እንደነበረ ነው (ዘሌ 12፡1-10)፡፡ አዳም በተፈጠረ በ40 ቀኑ፣ ሔዋንም በተፈጠረች በ80 ቀኗ ወደ ርስታቸው ገነት እንደገቡ ሕጻናትም በ40 እና በ80 ቀናቸው ተጠምቀው የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ወደሆነችው ወደ ቤተክርስቲያን ይገባሉ፡፡
በኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ህጻናት ወላጆቻቸው እንዲሁም ክርስትና እናት ወይም አባት ሃይማኖታቸውን ሊያስተምሯቸው ሃላፊነት ወስደው የክርስትና አባት ወይም እናት በተጨማሪ ቃል ገብተው ክርስትና በመነሳት (በመጠመቅ) የወላጆቻቸውን ርስት መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ። ከአርባ እና ከሰማንያ ቀን በኋላ የሚመጡ ተጠማቂዎች ግን ሃይማኖታቸውን ተምረው ካመኑ በኋላ በማንኛውም የዕድሜ ክልል መጠመቅ ይችላሉ። በሕይወት እስካሉ ድረስ መቸም ቢሆን ከመጠመቅ የሚያግዳችው ነገር የለም።
የክርስትና አባትና እናት
በ40 እና በ80 ቀናቸው ለሚጠመቁ ሕጻናት ስለ እምነታቸው ባለው ነገር ሁሉ ኃላፊነት የሚወስዱ የክርስትና አባትና እናት እንዲኖራቸው ያደረጉት በ4ኛው መ/ክ/ዘ የነበረው የቤተ ክርስቲያናችን የመጀመሪያው ኢጲስ ቆጶስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ናቸው። ዓላማውም መንፈሳዊ ዝምድናን (አበ ልጅነትን) ማጠናከሪያ መንገድ ነው። በአበ ልጅነት የተዛመዱ ሰዎች በጋብቻ መዛመድ አይችሉም። በሥጋ የተዛመዱ ከ7ተኛ የዝምድና ሐረግ በኋላ መጋባት የሚፈቀድ ሲሆን በአበ ልጅ ግን የተዛመደ ግን የቁጥር ገደብ የለውም (ፈጽሞ መጋባት አልተፈቀደለትም)፡፡ ይህም የሚያሳየው ከሥጋ ዝምድና ይልቅ ክብር የሚሰጠው ለመንፈሳዊ ዝምድና መሆኑን ነው።
ከክርስትና አባትነትና እናትነትን የሚከለክሉ ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም የሥጋ ዝምድና ያላቸው፣ የጋብቻ ዝምድና ያላቸው፣ ዕድሜያቸው ለማስተማር ለማሳመን ያልደረሰ፣ እምነት ትምህርት ችሎታ የሌላቸው፣ እምነታቸው ከተጠማቂው ጋር ተመሳሳይ ያልሆነ ናቸው፡፡ የጾታ ሁኔታ በተመለከተ ወንድ ወንድን ሴት ሴትን ያነሣል እንጂ ወንድ ሴትን፡ ሴት ወንድን ክርስትና ማንሣት አይፈቀድላቸውም፡፡ የክርስትና አባትና እናት ክርስትና ያነስዋቸው ልጆች በሥጋ ከወለድዋቸው ልጆች ሳይለዩ ሕጻናቱ ዕድሜያቸውም ለትምህርት ሲደርስ መሠረታዊ የሃይማኖት ትምህርት የማስተማር ግዴታ እንዳለባቸው ቃል ይገባሉ። በገቡት ቃል መሠረት በተግባር የመተርጎም ኃላፊነት አለባቸው።
ማዕተብ (ክር) ማሰር
ማዕተብ የሚለው ቃል ዐተበ ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም አመለከተ ማለት ነው። ስለዚህ ማዕተብ ማለት ምልክት ማለት ነው። በሃይማኖት አምነው ለተጠመቁ ክርስቲያኖች የሚሰጥ ምልክት (መታወቂያ) ወይም ማኅተም ነው። ስለ ማዕተብ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ምሳሌዎች ተጠቅሰዋል። በብሉይ ኪዳን የነበሩ አባቶች ለእምነታቸው መገለጫ ምልክት ነበራቸው። ለምሳሌ ለአበ ብዙኃን አብርሃም ግዝረት ተሰጥቶት ነበር (ሮሜ 4፡13 ፡ ዘፍ 17፡9-14)። ማዕተብ ክርስቶስ በገመድ መታሰሩንና መጎተቱን የሚያስታውስ ምልክትም ነው፡፡ "ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና (1ኛ ጴጥ 2:21)።" እንተባለ የክርስቶስን መከራ እናስብበታለን (ዮሐ 18፡12-24)።
ማዕተብ በሦስት ዓይነት ቀለም መሆኑ የሦስትነት (የሥላሴ) ምሳሌ ነው። ሦስቱ ክሮች ደግሞ በአንድ ተገምደው መሠራታቸው የአንድነቱ ምሳሌ ነው። ክርስቲያን ማዕተብ በማሰሩ ስለ ክርስቲያንነቱ ሳያፍር ይመሰክርበታል፤ አጋንንትን ድል ይነሣበታል፡፡ ተጸልዮበት ተባርኮ የሚታሠር ነውና ከቤተክርስቲያን በረከት ያገኝበታል፡፡ ማዕተብ ማሰርን ያስጀመረው ቅዱስ ያዕቆብ ዘእልበረዳኢ ክርስቲያኖችን ከመናፍቃን ለመለየት ማዕተብ ያስርላቸው እንነበር በመጻሕፍት ተጽፏል፡፡
የሚታይ አገልግሎት፤ የማይታይ ጸጋ
በምስጢረ ጥምቀት የሚታይ አገልግሎት ተጠማቂው ውሃ ውስጥ ብቅ ጥልቅ ሲል፤ ሥርዓተ ጸሎቱ ሲከናወን፤ ተጠማቂው ነጭ ልብስ ሲጎናጸፍ፣ ማዕተብ ሲያስር ወይም ሲታሰርለት ወዘተ. . . ነው፡፡ ይህም በዓይናችን ልናየው የምንችለው ነው፡፡ በምስጢረ ጥምቀት የሚገኝ የማይታይ ጸጋ ደግሞ ውኃው ወደ ማየ ገቦነት ሲለወጥ፤ ተጠማቂው የእግዚአብሔር ልጅነትን ሲያገኝ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ፡ ንጸሕናን ቅድስናን ገንዘብ ሲያደርግ ወዘተ. . . ናቸው፡፡ ምስጢረ ጥምቀትም በሚታይ አገልግሎት የማይታይ ጸጋ የሚገኝበት ልዩ ምስጢር ነው፡፡
የጥምቀት ምሳሌዎች
አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ወደ መልከጼዴቅ መሔዱ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም የምእመናን መልከጼዴቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ናቸው (ዘፍ. 14፡17)፡፡ ኢዮብ በዮርዳኖስ ተጠምቆ ከደዌው ተፈውሷል፡፡ ይህም ምእመናን ተጠምቀው ከደዌ ሥጋ ከደዌ ነፍስ የመፈወሳቸው ምሳሌ ነው፡፡ ንዕማን ሶርያዊ ተጠምቆ ከለምጽ ድኗል (2ነገ. 5፡14)፡፡ ይኸውም ምእመናን ተጠምቀው ከመርገመ ሥጋ ከመርገመ ነፍስ የመዳናቸው ምሳሌ ነው፡፡
የኖኅ መርከብ የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ. 7፥13)፡፡ ይኽንንም ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ "ጥቂቶች ማለት ስምንት ነፍሳት በውኃ የዳኑባትን መርከብ ሲሠራ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ትዕግሥት በዘገየ ጊዜ ቀድሞ ክደውት ለነበሩት ሰበከላቸው፡፡ አሁንም እኛን በዚያው አምሳል በጥምቀት ያድነናል ሥጋን ከዕድፍ በመታጠብ አይደለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመነሣቱ በእግዚአብሔር እንድናምን መልካም ግብርን ያስተምረን ዘንድ ነው እንጂ" (1ጴጥ. 3፥20) በማለት ገልጾታል፡፡ የጥፋት ውሃ በኖኅ ዘመን በበደላቸው ተጸጽተው ንስሓ ያልገቡ ሰዎችንና (ከኖኅና ቤተሰቡ እንዲሁም ለዘር እንዲቀሩ ከተደረጉት ፍጥረታት በቀር) በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ያጠፋው ማየ አይኅ (የጥፋት ውሃ) የጥምቀት ምሳሌ ሲሆን፤ ከጥፋት ውሃ የዳኑት ኖኅና ልጆቹ፤ ከክርስቶስ ጎን ለጥምቀታችን በፈሰሰው ትኩስ ውሃ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ከፍርድ ለሚድኑ ምዕመናን ምሳሌ ነው።
ለአብርሃም ሕግ ሆኖ የተሰጠው ግዝረት የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ አብርሃም ከአረጀ በኋላ ቢገረዝም ልጆቹ ግን በተወለዱ በስምንተኛው ቀን እንዲገረዙ እግዚአብሔር ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር (ዘፍ. 17፥9) "በሰው እጅ ያልተደረገ መገረዝን በእርሱ ሆናችሁ ተገረዛችሁ፡፡ በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችኋል በእርስዋም ከሙታን ለይቶ ባስነሣው በእግዚአብሔር ረዳትነትና በሃይማኖት ከእርሱ ጋር ተነሥታችኋል" (ቈላ. 2፥11)፡፡ ግዝረት ለጊዜው ለእስራኤል ዘሥጋ መለያ ሲሆን፤ ፍጻሜው ግን ሊመጣ ላለውና ለእሥራኤል ዘነፍስ ምዕመናን መክበሪያ ለሆነው ለጥምቀት ምሳሌ ነው።
የእስራኤል የኤርትራ ባህርን (ቀይ ባህርን) መሻገርም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፀ 14፡21። 1ቆሮ 10፡1)። ሙሴ የክርስቶስ፤ ባህሩን የከፈለባት በትር የመስቀል፤ ባህረ ኤርትራ የፍርድና የሲኦል፤ በተከፈለው ባህር የተሻገሩት እስራኤል በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ በጥምቀት ከእግዚአብሔር ተወልደው ባህረ ኃጢአትን የሚሻገሩ ምዕመናን ምሳሌ ነው። ኢያሱ የዮርዳኖስን ባህር ክፍሎ እስራኤል መሻገራቸውም እንዲሁ የጥምቀት ምሳሌ ነው (ኢያ 3፡14 4፡15)። ኢያሱ የክርስቶስ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት፤ ዮርዳኖስን የተሻገሩ እስራኤል በክርስቶስ አምነው በመጠመቅ የዳኑ ምዕመናን ምሳሌ ነው። የዮሐንስ ጥምቀት (ማቴ 3፡1) የአማናዊት ጥምቀት ምሳሌ ነበር። ዮሐንስ ህዝቡን የንስሓ ጥምቀት እያጠመቃቸው ከቆየ በኋላ ጌታ በሚመጣበት ጊዜ ግን እነሆ የእግዚአብሔር በግ በማለት ወደ ጌታ መርቷቸዋል ስለዚህ የዮሐንስ ጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ለአማናዊዉ የጌታ ጥምቀት የሚያዘጋጅ ነው፡፡
ጥምቀት አንዲት ናት!
የልጅነት ጥምቀት አንዲት ናት፤ አትደገምም (ኤፌ 4፡5) "ኃጢአት በሚሠረይባት አንዲት ጥምቀት እናምናለን" እንዲል፡፡ ከወላጆቻችን በሥጋ የምንወለደው አንድ ጊዜ ብቻ እንደሆነ ሁሉ ከውሃና ከመንፈስም ከእግዚአብሔር የምንወለደውም (የምንጠመቀው) አንድ ጊዜ ብቻ ነው። የጥምቀት ምሳሌ የነበረው ግዝረት አንድ ጊዜ ብቻ እንደነበረ ሁሉ ጥምቀትም አንድ ጊዜ ነው (ቆላ 2፥11)። ከጌታ ሥጋና ደም የምንሳተፍበት ምሥጢር በመሆኑ ጌታም የሞተውና የተነሳው አንድ ጊዜ ነውና አንድ ጊዜ ብቻ እንጠመቃለን (ሮሜ 6፡3)። በእኛ ቤተ ክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ በሌላ ሃይማኖት ገብቶ እንደገና ቢጠመቅ ወይም ከሌላ እምነት ተከታይ ጋር ጋብቻ ቢመሠርት በንስሓ ከተመለሰ በኋላ መጽሐፈ ቄደር ተጸልዮለት ይጠመቃል። ይህ ግን ሁለተኛ ጥምቀት ሳይሆን የንስሓ ጥምቀት ይባላል። ከኦሪየንታል አብያተ ክርስቲያናት (Oriental Churches) በቀር በሌላ ማንኛውም ቤተክርስቲያን ከተጠመቀ በኋላ አምኖ የሚመጣ ሰው ቢኖር እንደገና ይጠመቃል።
የሕፃናት ጥምቀት
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሕጻናትን በ40 እና በ80 ቀን ስታጠምቅ ምስጢራትን፣ ምሳሌዎችን፣ ትውፊትን እንዲሁም የጌታንና የሐዋርያትን አስተምህሮ መሠረት አድርጋ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም እንደሚናገረው ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ኃጢአትበደል አለባቸው ብላ ሳይሆን ከለጋነት ዕድሜያቸው ጀምረው ፍቅሩን እያጣጣሙ እንዲያድጉ የሚያስችላቸውን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ ልትሰጣቸው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሕጻናትን የምታጠምቀው ያውቃሉ ወይም አያውቁም ብላ አይደለም፡፡ የቤተሰቦቻቸውን እምነትና ፈቃድ ምስክር በማድረግ ነው እንጂ፡፡
- አዳምና ሔዋን በተፈጠሩ በ40 እና በ80 ቀናቸው ወደ ገነት መግባታቸው (ኩፋ 4፡9)፡፡
- እስራኤል መስዋዕት ይዘው በ40 እና በ80 ቀን ወደ ቤተመቅደስ እንዲመጡ መታዘዛቸው (ዘሌ 12፡1-8)፡፡
- በኦሪቱ ሕፃናትም አዋቂዎችም ተገርዘው የተስፋው ወራሾች ነበሩና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ 17፡1-5 ቆላ 2፡11-12)፡፡
- በባህረ ኤርትራ የተሸገሩት ሕፃናትም ጭምር ነበሩና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (1ኛ ቆሮ 10፡1-2)፡፡
- ወደ ኖኅ መርከብ የገቡት መላው ቤተሰብ ነውና ይህም የጥምቀት ምሳሌ ነው (ዘፍ 7፡1-17 1ኛ ጴጥ 3፡20-22)፡፡
- ሕፃናት በማኅፀን ሳሉ መንፈስ ቅዱስ ከሞላባቸው ሲወለዱ እንዳይጠመቁ የሚከለክለቸው ምንድን ነው (ሉቃ 1፡15 ኤር 1፡4-5)፡፡
- ሐዋርያትም ካስተማሩ በኋላ ቤተሰቡን ሙሉ ያጠምቁ ነበር (ሐዋ 10፡44-48 11፡13-14 16፡15 16፡43)፡፡
- ጌታችንም "ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ…" ያለው ሕፃናትንም ይመለከታል (ዮሐ 3፡8)፡፡
- ጌታችንም "ሕጻናት ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው" ብሏል (ማቴ 19፡14)፡፡
በአንዳንዶች ዘንድ የሕጻናት ጥምቀት ለዳግም ልደት ወይስ ለጥንተ አብሶ ስርየት? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በዚህ ላይ የጥንተ አብሶ ትርጉም ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት አለ፡፡ አንዳንዶች የሕጻናት ጥምቀት ጥንተ አብሶን ለማጥፋትና ልጅነትን ለማግኘት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጥንተ አብሶ ምክንያት የተጎዳውን የሰውን ባህርይ ለመጠገንና ልጅነትን ለማግኘት ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ጥንተ አብሶ በክርስቶስ ጠፍቶልናል፤ የሕጻናት ጥምቀት ለዳግም ልደት ብቻ ነው ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ሕጻናት ዳግም ልደትን ያገኙ ዘንድ መጠመቅ እንዳለባቸው ሁሉም ይስማማል፡፡
የሕጻናት ጥምቀት መብትን ይጋፋልን?
ጥምቀተ ክርስትና ሁል ጊዜ ተጠማቂው ተጠይቆ ላይፈጸም ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው ተጠማቂው ህጻን የሆነ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ለህጻናት የሚያስፈልጋቸውን እናደርግላቸዋለን እንጂ ፈቅደዋል (አልፈቀዱም) በሚል ግብዝነት ተይዘን ከጽድቅ ጉዞ እንዲለዩ አናደርግም፡፡ ይሁንና አንዳንዶች የሕጻናትን ጥምቀት መብተን መጋፋት አስመስለው ባለመረዳት ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያው ሰው አዳም የተፈጠረው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ሆኖ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረው በኋላ በአፍንጫው የሕይወት እስትንፋስን እፍ ብሎበታል፡፡ ይህም እፍታ ለአዳም የልጅነትን ጸጋ ያገኘበት ጥምቀቱ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ታሪክ በያዘው የኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ እግዚአብሔር ለአዳም የልጅነት ጸጋውን ከመስጠቱ በፊት እንደ ጠየቀው አይናገርም፡፡ ታዲያ እንዴት የሠላሳ ዓመቱ ጎልማሳ አዳም ያልተጠየቀውን ጥያቄ የአርባ ቀን ልጅ ጠይቁ ማለት ይቻላል? እግዚአብሔር አዳምን አልጠየቀውም ማለት አስገደደው ማለት አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ሕጻናትን በቀጥታ እነርሱን አልጠየቀችም ማለት አስገድዳቸዋለች ማለት አይደለም፡፡ አዳም የኋላ ኋላ በፈቃዱ ፈጣሪውን ክዶ ልጅነቱን እንዳጣ እንዲሁ የእግዚአብሔርን አባትነት ያልፈለጉትም አድገውም ቢሆን የመካድ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ምስጢረ ጥምቀት ከሥጋ የተወለደ ሰው ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልዶ የእግዚአብሔርን የጸጋ ልጅነት የሚያገኝበት ታላቅ ምስጢር ነው፡፡ ይህም ምስጢር ከሌሎች ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ቀዳሚው ስለሆነ "የክርስትና በር/መግቢያ" ይባላል፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢረ ጥምቀትን ራሱ ተጠምቆ አርአያ በመሆን፣ ጥምቀት ለመዳን አስፈላጊ መሆኑን በማስተማር፣ እንዲሁም ሐዋርያቱ እንዲያጠምቁ በማዘዝ መስርቶልናል፡፡ በዚህም መሠረት በሥላሴ ስም የተጠመቀ ሰውም አምላኩ ክርስቶስ፣ እምነቱ ክርስትና፣ ማንነቱ ክርስቲያን፣ እናቱ ቤተክርስቲያን ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምስጢረ ጥምቀትን የእምነት መሠረት በመሆኑ ከአምስቱ አዕማደ ምስጢራት፣ ተፈጻሚ ምስጢር በመሆኑ ከሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን በመመደብ ታላቅ ቦታ ትሰጣለች፡፡ የሰው ልጅ ሁሉ አምኖና ተጠምቆ በቀናችው የሃይማኖት መንገድ ተጉዞ ዘላለማዊ ሕይወትን ይወርስም ዘንድ የሕይወትን ቃል ትመግባለች፡፡ በጥምቀት ከማይጠፋ ዘር የወለደን፣ በሞቱና በትንሣኤው እንመስለው ዘንድ ተጠምቆ ተጠመቁ ያለን የቅዱሳን አምላክ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጥምቀት የተሰጠንን የልጅነት ጸጋ ይጠብቅልን፤ ለዚህ ጸጋ ያልበቁትን ወደ እግዚአብሔር መንግስት መግቢያ ያመጣልን ዘንድ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ጋብቻ
"መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር ነው።" ዕብ ፲፫፡፬
ጋብቻን ባርኮና ቀድሶ ለሰው ልጅ የሰጠው እግዚአብሔር ነው። በመሆኑም ጋብቻ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለምና የምትረዳው ጓደኛ እንፍጠርለት ብሎ እግዚአብሔር ሔዋንን ከአዳም አካል ፈጠራት። ዘፍ ፪፡፲፰። አዳምም ከአካሉ የተፈጠረችውን ሰው አይቶ እንዲህ አለ፡ "ይህች አጥንት ከአጥንቴ ይህች ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርሷ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል።" ዘፍ ፪፡፳፫-፳፭። እግዚአብሔር አምላክ ሰውን በመልኩ ፈጠረ። ወንድና ሴትም አድርጎ ፈጠራቸው። ከዚያም እንዲህ ብሎ ባረካቸው፡ "ብዙ ተባዙም፣ ምድርንም ሙሏት፣ ግዟትም፣ የባሕር አሦችና የሰማይ ወፎችን፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሁሉ ግዟቸው።" ዘፍ ፩፡፳፮-፴፩።
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ ተገልጦ ወንጌለ መንግሥትን እየሰበከ በዓለም ላይ በሚዘዋወርበት ወቅት ጋብቻ እጅግ የተቀደሰ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ በተቀደሰ ጋብቻ አንድ የሆኑ ተጋቢዎች በመንፈሳዊ ሕይወት የተሳሰሩ አንድ አካል መሆናቸውን ገልጿል፤ "የገዛ ሚስቱን የወደደ ራሱን ይወዳል፣ ማንም የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ከቶ የለምና" ሲል ባልና ሚስት አንድ አካል መሆናቸውን መስክሯል። ኤፌ ፭፡፳፩-፴፫። በሌላ መልእክቱም በሕገ ቤተክርስቲያን የተፈጸመ ጋብቻ ንጹሕና ክቡር መሆኑን አስተምሯል። ዕብ ፲፪፡፩-፮። ስለዚህ በሥርዓተ ተክሊል ማለት በቤተክርስቲያን ሥርዓት የሚፈጸም ጋብቻ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም የተባረከ በመሆኑ ሊፈርስ አይገባውም፤ "እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለየውም" ተብሎ የተሰጠው አምላካዊ ትእዛዝ ምንጊዜም መከበር አለበት። ማር ፲፡፩-፱። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረው ማንም ሰው ያለ ዝሙት ምክንያት ሚስቱን ቢፈታ እሷን አመንዝራ ወይም ዝሙት አዳሪ እንድትሆን ያደርጋታልና ሰውየው በደለኛ ይሆናል። ሴቲቱም ባልዋን ያለ ዝሙት ምክንያት ብትፈታውና ሰውየውም አመንዝራ ወይም ዘማዊ ቢሆን ለዚህ ኃጢአት ያበቃችው ሚስቱ ኃጢአተኛ ናት። ስለዚህ ባልና ሚስት ከኃጢአትና ከበደል ይድኑ ዘንድ በሕገ ቤተክርስቲያን አማካይነት የገቡትን የጋብቻ ቃል ኪዳን እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ጠብቀው መኖር ይገባቸዋል። በጋብቻቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ስም በቤተክርስቲያን የገቡትን ቃል ኪዳን ማፍረስ ዐቢይ ኃጢአትና ትልቅ በደል መሆኑን ምን ጊዜም መርሳት አይገባቸውም።
የጋብቻ ዓላማዎች ሦስት ናቸው
፩. መረዳዳት "የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት" ዘፍ ፪፡፲፰
የመጀመሪያው "የሚመቸውን ረዳት እንፍጠርለት" እንዲል ለመረዳዳት ነው። መረዳዳት ሲባልም በሥጋ ብቻ አይደለም በነፍስም ጭምር ነው። ለሥጋቸው በሥራ ሲረዳዱ ለነፍሳቸው ደግሞ በጸሎት ይረዳዳሉ። ለምሳሌ ይስሐቅ ሚስቱ ርብቃ ለሃያ ዓመታት መክና ልጅ አልወለደችለትም ነበር። በዚህም ምክንያት ስለ ርብቃ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ተለመነው፤ ርብቃም መንታ ፀነሰች ይላል። ዘፍ ፳፭፡፳፩።
፪. ከፍትወተ ሥጋ ለመጠበቅ ፩ኛ ቆሮ ፯፡፰-፱
ሁለተኛው ከፍትወተ ሥጋ ወይም ከዝሙት ለመጠበቅ ነው። ፩ኛ ቆሮ ፯፡፰-፱፤ ፩ኛ ቆሮ ፭፡፩፤ ምሳሌ ፮፡፴-፴፪።
፫. ዘር ለመተካት "ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት" ዘፍ ፩፡፳፰
ሦስተኛው ደግሞ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፤ እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው "ብዙ ተባዙ፤ ምድርንም ሙሏት" እንዲል ዘር ለመተካት ነው። ዘፍ ፩፡፳፰። እነዚህም እንደ ሦስት ጉልቻዎች የሚቆጠሩ ናቸው።
ከመጀመሪያው ጋብቻ ምን እንማራለን?
አዳምና ሔዋን ወደዚህ ዓለም ከመምጣታቸው በፊት እግዚአብሔር በሥጋም በነፍስም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አዘጋጅቶላቸዋል። ከሁሉም በላይ በጸጋ አክብሮአቸዋል። ፍጥረታት ሁሉ ይታዘዙላቸውና ይገዙላቸው ነበር። እግዚአብሔር በልግስና ከሰጣቸው ሀብት በስተቀር በራሳቸው ያመጡት የራሳቸው የሆነ ምንም አልነበራቸውም። ሁለቱም ዕርቃናቸውን ነበሩ። ትልቁ ሀብት እግዚአብሔር በአርአያውና በመልኩ ፈጥሮ የሰጣቸው አካል ነው። አዳም በአርባ ቀኑ ሔዋንም በሰማንያ ቀኗ ወደ ገነት የገቡት ይህን አካላቸውን ይዘው ነው። ከገነት በተባረሩም ጊዜ ከአካላቸው በስተቀር ይዘውት የወጡት ምንም ነገር የለም።
ስለዚህ ጋብቻን በምናስብበት ጊዜ ሁሉን ነገር እግዚአብሔር የሚያዘጋጅ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ለጋብቻ የመረጥነውም ሰው ዕራቁቱን ቢሆንም (ምንም ባይኖረው) እርሱነቱን ወይም እርሷነቷን ብቻ ለመቀበል መዘጋጀት አለብን። ወደዚህ ዓለም የመጣነው ዕርቃናችንን መሆኑን ለአፍታም መርሳት የለብንም። ዓለምን ጥለን የምንሄደውም ዕርቃናችንን ነው። ጻድቁ ኢዮብ "ከእናቴ ማኅጸን ራቁቴን ወጥቻለሁ ራቁቴንም ወደ ምድር እመለሳለሁ፤ እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔር ነሣ፣ እግዚአብሔርም እንደፈቀደ ሆነ፣ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን" ያለው ለዚህ ነው። ኢዮ ፩፡፳፩።
ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ
ፈቃደ እግዚአብሔር የሚጠየቀው በጸሎት ነው። አዳም ከሐዘን ጋር የጸለየው በኅሊናው ነው። በመሆኑም ከልብ መጸለይ ያስፈልጋል። "ፈቃድህ በሰማይ (በመላእክት ዘንድ) እንደሆነ እንዲሁም በምድር (በደቂቀ አዳም ዘንድ) ይሁን" ማለት ይገባል። ማቴ ፮፡፲። እንደ ፈቃዱም ስንለምነው ይሰማናል። ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ "በእግዚአብሔር ዘንድ ያለችን መውደድ ይህች ናት፤ በስሙ ከእርሱ ዘንድ የምንለምነውን ይሰማናልና። የምንለምነውንም እንደሚሰማን ካወቅን እንግዲያስ በእርሱ ዘንድ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን" ያለው ለዚህ ነው። ፩ኛ ዮሐ ፭፡፲፬።
ለምሳሌ ሁለት ማየት የተሳናቸው ሰዎች የዳዊት ልጅ ሆይ ማረን እያሉ በእምነት በለመኑ ጊዜ፣ "እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ" ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰላቸው፣ ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ ይላል። ማቴ ፱፡፳፯። ጥሩ የትዳር ጓደኞችም እንደ ዓይን ናቸው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል የትዳር ጓደኛን በዓይን መስሎ ተናግሯል። ማቴ ፲፰፡፱። በተጨማሪም የሰውነት መብራት ዓይን እንደሆነ፣ ዓይን ብሩህ ከሆነ ሰውነት ሁሉ ብሩህ እንደሚሆን፣ ዓይን ግን ታማሚ ከሆነ ሰውነት ሁሉ ጨለማ እንደሚወርሰው ተናግሯል። ማቴ ፮፡፳፪። ስለዚህ ትዳራችን በውስጥ በአፍአ ብርሃን እንዲሆን ዓይን የሆነ የትዳር ጓደኛ እንዲሰጠን በእምነት ከለመንነው ይሰማናል። ልመናችንን እንደሰማን ካወቅንና ካመንን የለመንነውን ሁሉ በጊዜው ይሰጠናል።
ሥርዓተ ተክሊልና ጸሎተ ተክሊል
የተክሊል ጋብቻ የሚፈጸመው ለሚከተሉት ተጋቢዎች ነው፦
- ሥጋዊ ድንግልና ላላቸው
- የሃይማኖት አንድነት ላላቸው
- ለአቅመ አዳም ለደረሱ
- ፈቃደኝነታቸውን ለገለጹ ተጋቢዎች
ጸሎተ ተክሊል ከቅዳሴ በፊት የሚፈጸም ሲሆን ያለሥጋ ወደሙም አይፈጸምም። የተክሊል ጋብቻን ለመፈጸም ሁለቱም ተጋቢዎች ድንግል መሆን ያለባቸው ሲሆን ነገር ግን ተጋቢዎቹ ከጋብቻ በፊት በግብረ ሥጋ የሚተዋወቁ ከሆነ በተክሊል መጋባት አይችሉም። ሆኖም ግን በቤተክርስቲያንና በሥርዓተ ቁርባን ለመጋባት ምንም የሚያግዳቸው ነገር የለም፤ ንስሐ እስከገቡ ድረስ።
ደናግላን ላልሆኑ ተጋቢዎች የሚደረገው ሥርዓት የመአስባን ጋብቻ ይባላል። ይህ ጋብቻ ከተክሊል ጋብቻ ሥርዓቱ የሚለይ ሲሆን በተክሊል እንደሚደረገውም ለተጋቢዎቹ በራሳቸው ላይ አክሊል አይደረግላቸውም። ይህ ለድንግልናቸው እንደመንፈሳዊ ሽልማት የሚሰጥ አክሊል ሲሆን ለመአስባን ተጋቢዎች ይህ አለመኖሩ ጋብቻቸውን የተቀደሰ ጋብቻ ከመሆን አያግደውም። እንዲያውም በትክክል እና ከልብ በመሆን ንስሐ ከገቡ መላእክት በስውር በአካለ ነፍሳቸው ራስ ላይ የድል አክሊልን ያቀዳጁአቸዋል። ምክንያቱም ንስሐ የነፍስ ድንግልናን ታስመልሳለችና።
ለተጋቢዎች ምክር
የተወደዳችሁ ምዕመናን ታዲያ ይህንን ሥርዓት ለመፈጸምና በሥርዓተ ተክሊል የሚገኘው መንፈሳዊ በረከት እንዳይቀርብን ከፈለግን እውነተኛ ንስሐ ያስፈልገናል። ያም ማለት ከጋብቻ በፊት በግብረ ሥጋ መተዋወቃችን በፍጹም በቤተክርስቲያን ሥርዓት የማይደገፍ መሆኑን ተገንዝበን ከልብ በመጸጸት እግዚአብሔርን እንዳሳዘንን በማመን ንስሐ መግባት ይኖርብናል። ከንስሐ አባቶቻችን ጋር በመወያየት ከዚህ ውጭ የሠራነውንም ሌሎች ኃጢአታችንን በመናዘዝ ነፍሳችንን ፍጹም ንጹሕ አድርገን ለጋብቻ መዘጋጀት ይኖርብናል።
የሚሰጠንን ቀኖና (ለምሳሌ የጾም፣ የስግደት ወይም የምጽዋት ትእዛዝ) በሚገባ በመፈጸም ከእንባ ጋር የንስሐ ጸሎት ወደ ፈጣሪያችን በማቅረብ የነፍሳችንን ድንግልና ማስመለስ አለብን። ከዚያ በኋላ ነው ጋብቻችንን መፈጸም የሚኖርብን። ከተጋባንም በኋላ ከሥጋ ወደሙ መራቅ የለብንም። ባመቸን ጊዜ ሁሉ በሰንበት ወይም በበዓላት ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ ከትዳር አጋራችን ጋር መቀበል አለብን። ይህ ካልሆነ የጋብቻችን ዕለት ብቻ የተቀበልነው ሥጋና ደሙ ለፈተና እንዳይዳርገን ልንጠነቀቅ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ሰይጣን ሁል ጊዜም ቢሆን ሥጋውንና ደሙን የተቀበሉ ሰዎች ደግመው እንዳይቀበሉ ለማድረግ በጣም ይጥራልና ነው።
ምክረ ካህን
"የሚመክር ቢሆን በመምከሩ ይትጋ" ሮሜ 12፥6-8
መንፈሳዊ የምክር አገልግሎት ከእግዚአብሔር በተሰጠ ጸጋ የሚከናወን መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልዕክቱ ምዕራፍ 12 ላይ ገልጾአል። በቅድስት ቤተክርስቲያን በዓውደ ምሕረት በስብከት እና በተለያዩ መርሐግብሮች ከምንሰጠው የሰውን ልጆች የመቅረጽ እና የዘለዓለማዊ መንገድን የማሳየት አገልግሎት በተጨማሪ መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ይኸውም በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች በማኀበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች የተጠመዱ ስለሆነ ነው፡፡
የመንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት አስፈላጊነት
ሥነ-ልቦናዊ እርዳታ ስለሆነ
ቅዱስ ጳውሎስ "ከእናንተ እያንዳንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም" ገላ 6፥1 ብሎ እንዳስተማረው የሰዎችን ሸክም ከምናቀልበት እርዳታ ዋነኛው ምክክር ነው። ከአካላዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ እገዛ የበለጠ የሥነ-ልቦና እገዛ ወሳኝ ነው፡፡ የሰው ልጅ ገንዘብና እውቀት ይዞ ደስታና መረጋጋት ከሌለው ምን ዋጋ አለው? ስለዚህም ከቀቢጸ ተስፋ እንዲወጡ፣ በእግዚአብሔር እንዲታመኑ፣ ደስታ የተሞላበት ሕይወት እንዲመሩ ለማስቻል መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡
በግልና በጥልቀት የሚደረግ ስለሆነ
በርካታ አገልግሎቶቻችን በአደባባይ ሲሆኑ ምክክር ግን ተመካካሪና አመካካሪ (ካህን) ለብቻቸው ሆነው ጥልቅ ችግሮችን እና መፍትሔዎች ላይ ስለሚመካከሩ እጅግ ውጤታማ ነው፡፡ በአደባባይ አገልግሎት እያንዳንዱ ሰው ተምሮ ለለውጥ ቢዘጋጅም ነገር ግን ስለ ችሎታው፣ ችግሮቹ፣ መፍትሔዎቹ ወ.ዘ.ተ የመነጋገር አጋጣሚ የሚያገኘው እና በዓውደ ምሕረት የተማረውን በሕይወቱ የሚተገብረው በምክክር ሲታነጽ ብቻ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
ምሥጢር የሚጠብቅ ስለሆነ
የዚህ አገልገሎት አማካሪው (ካህን) ለምክክር የመጣውን ሐሳብና ችግር በምሥጢር የመጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ አለበት፡፡ ይህም በመሆኑ ተመካካሪው ችግሩን ሳይፈራና ሳይጠራጠር መግለጽ የሚችልበት የምክክር አገለግሎትና መፍትሔ ማግኛ በመሆኑ ውጤታማ ነው፡፡ በአደባባይና ላላመኑበት ሰው ሊያወያዩት የማይችሉትን የውስጥ ችግር ሊቀርፍ የሚችል ተግባር ከመንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት በይበልጥ በንስሐ አባትና ልጅ መካከል እንደሚፈጸመው አገልግሎት የተሻለ አይኖርም፡፡
በአጠቃላይ ምክክር እጅግ አስፈላጊ ሲሆን ነገር ግን ካህናትም ሆንን የተለያዩ የቤተክርስቲያን የአገልግሎት ክፍሎች ትኩረት ሰጥተነው ስንተገብር በብዛት አንታይም። በግብጽ ቤተክርስቲያን የምክክር አገልግሎት ተቋም እንደተደራጀ እና ካህናትም በቤተክርስቲያን መርሐ ግብር ተመድቦላቸው ለረጅም ሰዓት ሲመክሩ እንደሚውሉ ምሥክሮች ይናገራሉ። ቢቻለን በሰ/ት/ቤቶችና በስብከተ ወንጌል ክፍሎች ውስጥ እንደዚሁም መንፈሳዊ አገልግሎት ሰጪ ማኅበራት መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት ክፍሎች አቋቁመን ካህናት አባቶች እና በምክክር ደረጃ ወደ ካህናት ሊያደርሱ የሚችሉ ጸጋው እና ችሎታው ያላቸው አገልጋዮች በማሳተፍ ብንተጋ ለቤተክርስቲያን ሆነ ለሐገራችን መልካም ፍሬ እናፈራለን። እንደዚሁም አደራችንን በመወጣት መንፈሳዊ ዋጋ እንደምናገኝበት የታመነ ነውና፡፡ "የሚመክር ቢሆን በመምከሩ ይትጋ" ሮሜ 12፥6-8
ምክክርና መንፈሳዊ የምክክር አገልግሎት ምንነት
በሰው ልጆች ኑሮ ውስጥ ሃዘንና ደስታ መከሰታቸው የማይቀር ነው። በእያንዳንዱ የእድገት ዘመናችን የተለያዩ ችግሮች በተፈጥሮአዊና በአካባቢያዊ ምክንያት ያጋጥመናል፡፡ ለችግሩም ቶሎ መፍትሄ ካልፈለግን በጤና በሥራ በማኀበራዊ እና መንፈሳዊ ኑሮአችን ላይ ተጽዕኖ ያመጣብናል፡፡ በመሆኑም ችግራችንን አስወግደን ጤናማ ኑሮ ለመምራት አንዱ መፍትሄ ምክክር ነው፡፡
ምክክር ምንድነው?
ምክክር እንደ ሥነ-ልቦና የምሁራን አገላለጽ ለአንድ ወይም ከዚያ በላይ ለሆኑ ሰዎች ለችግራቸው በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ የሚደረግ ውይይት (ግንኙነት) ነው፡፡
ምክክር ሰዎች በተፈጥሮ በትምህርትና በልምድ ያገኙትን አቅም በአግባቡ መጠቀም፣ ችግሮች እንዳይገጥማቸው በመከላከልና የሚገጥማቸውንም ችግሮች ለመቋቋም፣ ለራሳቸውና ለወገናቸው ትርጉም ያለውን ሥራ እንዲሰሩና ሕይወታቸው የተሳካ እንዲሆን መረዳት ወይም ማገዝ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሰዎች ችሎታቸውን እንዲያውቁና እንዲያሳድጉ የሚያስችል ነው፡፡ በምክክር አገልገሎት ውስጥ ምክክርን የሚመራው "አመካካሪ" ሲባል መፍትሄ ፍለጋ የመጣው "ተመካካሪ" (Client) በመባል ይታወቃል፡፡
የምክክር አገልግሎት ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው አመካካሪው የተመካካሪውን ችግር ከነመንስዔው አጣርቶ ተመካካሪው እራሱ ችግሩን ከአመካካሪው የሚደረግለት እገዛ ተጠቅሞ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ ማድረግ ነው፡፡
የምክክር ግብ
እንደ መስኩ ባለሞያዎች አገላለጽ ምክክር ጠንካራ ግብ ያለው መሆኑን በመግለጽ የሚከተሉት መሆናቸውን ያስገነዝባሉ፡፡
- ተመካካሪው በደረሰበት ችግር የጠባይ ለውጥ እንዲያመጣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣
- የችግር መቋቋሚያ ዘዴዎችን እንዲያዳብር ማድረግ፣
- ተመካካሪው እምቅ እውቀቱንና አቅሙን መጠቀም እንዲችል ማበረታታት፣
- ተመካካሪው በራስ መተማመንን እንዲያዳብር መርዳት፣ እራሱን እንዲሆን ማድረግ እና የመሳሰሉት ግቦች ያሉት ነው፡፡
የምክክር ዓይነቶች
ምክክር ከሥነ-ልቦና ትምህርት አንዱ ክፍል ሲሆን ዓይነቶቹም በርካታ ስለመሆናቸው ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ከእነሱም ውስጥ፦
- የቤተሰብ ምክክር አገልግሎት (የቤተሰብ አባላት ባሉበት የሚደረግና ችግራቸው እንዲፈታ የማማከሪያ ሂደት ነው)
- የጋብቻ ምክክር
- የወጣቶችና የሕጻናት ምክክር
- የአካል ጉዳተኞች ምክክር
- የውሳኔ አሰጣጥ ምክክር
- የትምህርት ምክክር
- የሥራና የሞያ ምክክር
- የሐዘን ምክክር
- የመንፈሳዊ ምክክር አገልግሎት
ጸሎተ ቅዳሴ
ቤተ ክርስቲያናችን ሥጋ ወደሙን የምታከብርበት የተለየ ሥርዓተ ጸሎት አላት፡፡ ይህ ልዩ የምስጋና ጸሎት "ጸሎተ ቅዳሴ" ይባላል። ያለ ጸሎተ ቅዳሴ ሥጋ ወደሙ አይዘጋጅም (አይፈተትም)፡፡ ያለ ሥጋ ወደሙም ቅዳሴ አይቀደስም፡፡ ቅዳሴ ማለት ቀደሰ አመሰገነ ከሚለው ግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ማመስገን ምስጋና ማለት ነው። ሰው ከተፈጠረበት አላማ አንዱ ለማመስገን ነውና በተለየ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በሰንበት ቀን አለማስቀደስ ንስሓ የሚያስፈልገው ኃጥአት ነው።
በቤተ ክርስቲያን የታወቁና እስከ አሁንም በአገልግሎት ላይ ያሉ ቅዳሴያት በዓይነት 14 ሲሆኑ ቀደም ባሉት ዘመናት በተለይ በወርኀ ጽጌ ይቀደስ የነበረ "መዓዛ ቅዳሴ" የሚባል 15ኛ ቅዳሴም በቤተ ክርስቲያናችን ይገኛል፡፡
በቅዳሴ ግዜ ትምህርት፣ ታሪክ፣ ተግሳጽ ተካቶበታል። ቅዳሴ ከቤተክርስቲያን ውጪ የትም አይከናወንም። የቅዳሴ አገልግሎት በካህናት፣ በዲያቆናት፣ በምዕመን በጋራ በቅብብሎሽ እና በዜማ የሚከናወን ነው።
በቅዳሴ ውስጥ 7 የማሳረጊያ ጸሎት ይደረጋል፤ 4 የኑዛዜአት ግዜአት አሉ፤ በቅዳሴ ግዜ 2 ግዜ ይሰገዳል፤ 42 ግዜ ቡራኬያት፣ 25 ጊዜ ጸልዮ፣ 14 ግዜ ለጸሎት ተነሱ ይባላል። ከምግብና ከውሃ በመከልከል በባዶ ሆድ የሚጸለይ ጸሎት ነው።
በቅዳሴ መግቢያ አስቀድሞ የዮሐንስ መጥምቁ አዋጅ ነጋሪት ቃል ይታወሳል (ወደ ቅዳሴ ሲገቡ የሚደወለው ደውል)። ካህናት ከቤተልሔም እስከ ቤተ መቅደስ ድረስ ተሸክመው ከኃላ ይከተላሉ (ጌታ በቤተልሔም ተወልዶ እስከ ቀራንዮ ድረስ የተጓዘውን ለማስታወስ)። ቀራንዮ ላይ እራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ቤተመቅደስ ላይም ሥጋና ደሙ በካህናት በኩል ለምዕመናን ይቀርባል። "ሥጋየን የበላ ደሜንም የጠጣ የዘላለም ህይወት አለው" (ዮሐንስ ወንጌል 6፡54) እንዲል።
ይህ ልዩ የቅዳሴ ምስጢር ለእኛ ነውና የተዘጋጀው ዘወትር ለማስቀደስ እንሩጥ። አምላካችን እግዚአብሔር ከቅዳሴው በረከት አይለየን። የቅዱሳን ጸሎታቸው በረከታቸው ይደርብን፡፡
ጸሎተ ፍትሐት
ጸሎተ ፍትሐት ለበደሉት ሥርየት ኃጢአትን፣ ይቅርታን፣ ዕረፍተ ነፍስን ያሰጣል፡፡ ለደጋጎች ደግሞ ክብርን፣ ተድላን፣ ዕረፍትን ያስገኛል፡፡
ሙታንና ሕያዋን የሚገናኙት በጸሎት አማካኝነት ነው፡፡ ሕያዋን ለሙታን ይጸልያሉ፤ ሙታንም ለሕያዋን ይለምናሉ፡፡ (ሄኖ. 12፤34) ሕያዋን ለሙታን የሚጸልዩት ጸሎትና የሚያቀርቡት መሥዋዕት በግልጽ እንደሚታይ ሁሉ ሙታንም በአጸደ ነፍስ ሆነው በዚህ ዓለም ለሚቆዩ ወገኖቻቸው ሕይወትና ድኅነትን፣ ስርየተ ኃጢአትንና ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን፣ ጽንዓ ሃይማኖትን እንዲሰጣቸው፣ በንስሐ ሳይመለሱ፣ ከብልየተ ኃጢአት ሳይታደሱ እንዳይሞቱ ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ፡፡ ይህም ሥርዓት እስከ ዕለተ ምጽአት ሲፈጸም የሚኖር ነው፡፡
ለሙታን ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፣ መሥዋዕት እንዲቀርብላቸው በቤተ ክርስቲያንና በመካነ መቃብራቸው እንዲጸለይላቸው ቅዱሳን ሐዋርያት በቀኖና ሐዋርያት አዝዘዋል፡፡ "በክርስቶስ አምነው ስለሞቱ ወንድሞቻችሁ ክርስቲያኖችና ሰማዕታት በቤተ ክርስቲያን ያለሐኬት ተሰብሰቡ፡፡ በቤተ ክርስቲያን መሥዋዕት ሠውላቸው፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወደ መቃብር ስትወስዱአቸውም መዝሙረ ዳዊት ድገሙላቸው፡፡" (ዲድስቅልያ አንቀጽ 33 ገጽ 481)
ነቢዩ ዳዊትም "የጻድቅ ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ነው፡፡ ነፍሴ ሆይ ወደ ዕረፍትሽ ተመለሽ፣ እግዚአብሔር ረድቶሻልና፣ ነፍሴን ከሞት አድኖአታልና፡፡" በማለት ሙታን በጸሎት፣ በምስጋና፣ በመሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር እንዲሸኙ በመዝሙሩ ተናግሯል፡፡ (መዝ. 115፤114-7)
የቤተ ክርስቲያን የሕግና የሥርዓት መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥትም በፍትሕ መንፈሳዊ በዲድስቅልያ የተጠቀሰውን ያጸናል፡፡ (አንቀጽ 22) ስለ ሙታን የሚጸለየው መጽሐፈ ግንዘትም ካህናት ለሞቱ ሰዎች ሊጸልዩላቸው፣ በመሥዋዕትና በቁርባን ሊያስቧቸው ይገባል ይላል፡፡ ካህናት ጸሎተ ፍትሐት በሚያደርጉላቸው መሥዋዕት እና ቁርባን ስለ እነርሱ በሚያቀርቡላቸው ጊዜ መላእክት ነፍሳቸውን ለመቀበል ይወርዳሉ፡፡ ኃጢአተኞች ከሆኑ ስለ ሥርየተ ኃጢአት ይለምኑላቸዋል፤ ይማልዱላቸዋል፡፡ ንጹሐንም ከሆኑ ደስ ይላቸዋል፡፡ "ሰውን ለወደደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ክብር ምስጋና ይገባል፣ በምድርም ሰላም፡፡" እያሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ ይህም የመላእክት ምስጋናና ደስታ ስለ ሰው ልጅ ድኅነት ነው ተብሎ ተጽፎአል፡፡
የደጋግ ሰዎችን ነፍሳት ቅዱሳን መላእክት እንደሚቀበሏቸው በቅዱስ ወንጌል ተጽፎአል፡፡ "አልዓዛርም ሞተ፤ መላእክትም ወደ አብርሃም ዕቅፍ ወሰዱት፡፡" (ሉቃ. 16፤22)
ጸሎተ ፍትሐት የዘሐን ጊዜ ጸሎት ነው፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ "በእናንተ ባለው መሠረት ከመንጋው መካከል በሞተ ሥጋ የተለዩትን ምእመናን በጸሎትና በዝማሬ እንሸኛቸዋለን፡፡" (ያዕ. 5፤13) ጸሎተ ፍትሐት የሚደረገው ለከሀድያንና ለመናፍቃን ሳይሆን ለሃይማኖት ሰዎች ነው፡፡
"ማንም ወንድሙን ሞት የማይገባውን ኃጢአት ሲያደርግ ቢያየው ይለምን፣ ሞትም የማይገባውን ኃጢአት ላደረጉት ሕይወት ይሰጥለታል፡፡ ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፡፡ ስለዚህ እንዲጠይቅ አልልም፡፡ ዓመፃ ሁሉ ኃጢአት ነው፡፡ ሞትም የማይገባው ኃጢአት አለ፡፡" (ዮሐ. 5፤16) ለምሳሌ በተለያየ መንገድ ራሱን ለገደለ ሰው ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ምክንያቱም ቤተ መቅደስ ሰውነቱን በገዛ እጁ አፍርሷልና፡፡ "የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖራችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፡፡ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ነውና ያውም እናንተ ናችሁ፡፡" ይላልና፡፡ (1ቆሮ. 3፤16) እንዲሁም ለመናፍቃን፣ ለአረማውያንም ጸሎተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ምክንያቱም ብርሃን ከጨለማ ጋር አንድነት የለውምና፡፡ (2ቆሮ. 6፤14)
ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጅ የማትጸልይበት ጊዜ የለም፡፡ ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት ከመጸነሱ በፊት የተባረከ ጽንስ እንዲሆን እንደ ኤርምያስ በማኅፀን ቀድሰው (ኤር. 1፤5) እንደ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ በማኅፀን መንፈስ ቅዱስን የተመላ አድርገው እያለች ትጸልያለች፡፡ በወሊድ ጊዜም ችግር እንደያጋጥመው ትጸልያለች፣ በጥምቀትም የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሆን ትጸልያለች፣ ታጠምቃለች፡፡ በትምህርት እየተንከባከበች ጸጋ እግዚአብሔርን እየመገበች ታሳድጋለች፡፡ እርሷ የጸጋው ግምጃ ቤት ናትና፡፡ በኃጢአት ሲወድቅም ኃጢአቱ እንዲሠረይለት ንስሐ ግባ ትለዋች፡፡ እንዲሠረይለትም ትጸልያለች፡፡ በሞቱም ጊዜ እግዚአብሔር ኃጢአቱን እንዳይዝበት በደሉን እንዳይቆጥርበት ትጸልይለታለች፡፡ እንዲህ እያደረገች የእናትነት ድርሻዋን ትወጣለች፡፡ አንድ ሰው ሲሞት ዘመድ አዝማድ በዕንባ ይሸኘዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ዕንባዋ ጸሎት ነውና በጸሎቷ የዚያን ሰው ነፍስ ለታመነ ፈጣሪ አደራ ትሰጣለች፣ ነፍሳቸውን ተቀበል ብላ ትጸልያለች፡፡
ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐትን የምታደርገው ይሆናል ይደረጋል ብላ በፍጹም እምነት ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን እስከ መጨረሻ ተስፋ አይቆርጥምና፡፡ "ወኵሎ ዘሰአልክሙ በጸሎት እንዘትትአመኑ ትነሥኡ፡፡ በሃይማኖት ጸንታችሁ የለመናችሁትን ሁሉ ታገኛላችሁ፡፡" (ማቴ. 21፤22) "ስለዚህ እላችኋለሁ፤ የጸለያችሁትን ሁሉ እንዳገኛችሁ እመኑ ይሁንላችሁማል፡፡" (ማር. 11፤24) "ለምኑ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ ታገኛላችሁ፤ መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችሁማል፤ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና የሚፈልገውም ያገኛል፡፡ መዝጊያውንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡" (ማቴ. 7፤7) "በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ፤ ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ፡፡" (ዮሐ. 14፤13) ይላልና፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስም በመልእክቱ "የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታወቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ፡፡ በእርሱ ዘንድ ያለን ድፍረት ይህ ነው፡፡ እንደ ፈቃዱ አንዳች ብንለምን ይሰማናል፡፡ የምንለምነውንም እንዲሰማልን ብናውቅ ከእርሱ የለመነውን ልመና እንደተቀበልን እናውቃለን፡፡" (ዮሐ. 5፤3) ብሏል፡፡ እንግዲህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቷ ሙሴን ከመቃብር አስነሥቶ ፊቱን ያሳየ አምላክ (ማቴ 17፤3) ለእነዚህም ሳይንቃቸው የምሕረት ፊቱን ያሳያቸዋል የሚል ነው፡፡ መሐሪ ይቅር ባይ ለሆነው አምላክ የሚሳነው ነገር የለምና፡፡ (ዘፍ. 18፤13፣ ሉቃ. 1፤37)
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ "ሞት የሚገባው ኃጢአት አለ፤ ስለዚህ እንዲጠይቅ አልልም" እንዳለ ቤተ ክርስቲያንም የምትከተለው ይህንኑ ነው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቷቸው ከኃጢአት መመለስ ከበደል መራቅ፣ ንስሐ መግባት፣ ሥጋወደሙን መቀበል ሲችሉ በሕይወታቸውና በእግዚአብሔር ቸርነት እየቀለዱ መላ ዘመናቸውን የሚያሳልፉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህም በራሳቸው ላይ የፈረዱ ናቸው፡፡ ደግሞም "ስሞት በጸሎተ ፍትሐት ኃጢአቴ ይሰረይልኛል" ኃጢአትንም አልተውም ማለት በእግዚአብሔር መሐሪነት መቀለድና እርሱንም መድፈር ስለሆነ ይህም ሞት ከሚገባው ኃጢአት የሚቆጠር ነው፡፡
እንግዲህ ለበጎ የተሠራልንን ጸሎተ ፍትሐት ክብር የምናገኝበት ያደርግልን ዘንድ የእግዚአበሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡ ሃይማኖት የለየንን መቃብር አንድ አያደርገንም፤ ገጽ 20